፲
፩ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤
፪ ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤
፫ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መብል በሉ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤
፬ ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዓለት ጠጥተዋልና፥ ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ።
፭ እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ በሚበዙት ደስ አላለውም፥ በምድረ በዳ ወድቀዋልና።
፮ እነዚህም ክፉ ነገር እንደ ተመኙ እኛ ደግሞ እንዳንመኝ ይህ ምሳሌ ሆነልን።
፯ ሕዝብም ሊበሉ ሊጠጡም ተቀመጡ ሊዘፍኑም ተነሡ ተብሎ እንደ ተጻፈ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ።
፰ ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ በአንድ ቀንም ሁለት እልፍ ከሦስት ሺህ እንደ ወደቁ አንሴስን።
፱ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑት በእባቦቹም እንደ ጠፉ ጌታን አንፈታተን።
፲ ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጎራጎሩ በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጐርጕሩ።
፲፩ ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ።
፲፪ ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።
፲፫ ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።
፲፬ ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ።
፲፭ ልባሞች እንደ መሆናችሁ እላለሁ፤ በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ።
፲፮ የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን?
፲፯ አንድ እንጀራ ስለ ሆነ፥ እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን፤ ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።
፲፰ በሥጋ የሆነውን እስራኤል ተመልከቱ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉ የመሠዊያው ማኅበረተኞች አይደሉምን?
፲፱ እንግዲህ ምን እላለሁ? ለጣዖት የተሠዋ ምናምን ነው እላለሁን? ወይስ ጣዖት ምናምን እንዲሆን እላለሁን?
፳ አይደለም፤ ነገር ግን አሕዛብ የሚሠዉት ለአጋንንት እንዲሆን እንጂ ለእግዚአብሔር እንዳይሠዉ እላለሁ፤ ከአጋንንትም ጋር ማኅበረተኞች እንድትሆኑ አልወድም።
፳፩ የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም።
፳፪ ወይስ ጌታን እናስቀናውን? እኛስ ከእርሱ ይልቅ እንበረታለንን?
፳፫ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም።
፳፬ እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ።
፳፭ በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ ብሉ፤
፳፮ ምድርና በእርስዋ የሞላባት ሁሉ የጌታ ነውና።
፳፯ ከማያምኑ ሰዎች አንዱም ቢጠራችሁ ልትሄዱም ብትወዱ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ የሚያቀርቡላችሁን ሁሉ ብሉ።
፳፰ ማንም ግን። ይህ ለጣዖት የተሠዋ ነው ቢላችሁ ከዚያ ካስታወቃችሁና ከሕሊና የተነሣ አትብሉ፤
፳፱ ስለ ባልንጀራህ ሕሊና እንጂ ስለ ገዛ ሕሊናህ አልናገርም። አርነቴ በሌላ ሰው ሕሊና የሚፈርድ Avረ ስለ ምንድር ነው?
፴ እኔም በጸጋ ብበላ፥ በነገሩ ስለማመሰግንበት ስለ ምን እሰደባለሁ?
፴፩-፴፫ እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት።