፮
፩ ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በዓመፀኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን?
፪ ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ ብትፈርዱ ከሁሉ ይልቅ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ አትበቁምን?
፫ የትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንድንፈርድ አታውቁምን?
፬ እንግዲህ ስለ ትዳር ጉዳይ የፍርድ ቤት ቢያስፈልጋችሁ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጆች አድርጋችሁ ታስቀምጣላችሁን?
፭ አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ። እንደዚህ ነውን? በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን?
፮ ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል፥ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋልን?
፯ እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን?
፰ ነገር ግን እናንተ ትበድላላችሁ ታታልሉማላችሁ፥ ያውም ወንድሞቻችሁን።
፱ ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ
፲ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።
፲፩ ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል።
፲፪ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን አይጠቅምም። ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሠለጥንብኝም።
፲፫ መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሥጋ ነው፤
፲፬ እግዚአብሔርም ጌታንም አስነሣ እኛንም በኃይሉ ያስነሣናል።
፲፭ ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደ ሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን? አይገባም።
፲፮ ወይስ ከጋለሞታ ጋር የሚተባበር አንድ ሥጋ እንዲሆን አታውቁምን? ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ ተብሎአልና።
፲፯ ከጌታ ጋር የሚተባበር ግን አንድ መንፈስ ነው።
፲፰-፳ ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል።