፱
፩ ለቅዱሳን ስለሚሆነው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልግምና፤
፪ በጎ ፈቃዳችሁን አውቄአለሁና፤ ስለዚህም። አካይያ ከአምና ጀምሮ ተዘጋጅቶአል ብዬ ለመቄዶንያ ሰዎች በእናንተ እመካለሁ፥ ቅንዓታችሁም የሚበዙቱን አነሣሥቶአል።
፫ ነገር ግን ለእነርሱ እንዳልሁ፥ የተዘጋጃችሁ ትሆኑ ዘንድ በዚህም ነገር ስለ እናንተ ያለው ትምክህታችን ከንቱ እንዳይሆን ወንድሞችን እልካለሁ፤
፬ ምናልባት የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር ቢመጡ፥ ያልተዘጋጃችሁም ሆናችሁ ቢያገኙአችሁ፥ እናንተ እንድታፍሩ አላልንም እኛ ግን በዚህ እምነታችን እንድናፍር አይሁን።
፭ እንግዲህ እንደ በረከት ሆኖ ከስስት የማይሆን ይህ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ አስቀድመው ወደ እናንተ መጥተው፥ አስቀድማችሁ ተስፋ የሰጣችሁትን በረከት አስቀድመው እንዲፈጽሙ ወንድሞችን እለምን ዘንድ እንዲያስፈልገኝ አሰብሁ።
፮ ይህንም እላለሁ። በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፥ በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል።
፯ እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።
፰-፲ ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤
፲፩ በእኛ በኩል ለእግዚአብሔር የምስጋና ምክንያት የሚሆነውን ልግስና ሁሉ እንድታሳዩ በሁሉ ነገር ባለ ጠጎች ትሆናላችሁ።
፲፪ የዚህ ረድኤት አገልግሎት ለቅዱሳን የሚጎድላቸውን በሙሉ የሚሰጥ ብቻ አይደለምና፥ ነገር ግን ደግሞ በብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይበዛል፤
፲፫ በዚህ አገልግሎት ስለ ተፈተናችሁ፥ በክርስቶስ ወንጌል በማመናችሁ ስለሚሆን መታዘዝ እነርሱንና ሁሉንም ስለምትረዱበት ልግስና እግዚአብሔርን ያከብራሉ፥
፲፬ ራሳቸውም ስለ እናንተ ሲያማልዱ፥ በእናንተ ላይ ከሚሆነው ከሚበልጠው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ይናፍቁአችኋል።
፲፭ ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።