1ኛ የዮሐንስ መልእክት
፩
፩ ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤
፪ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤
፫ እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው።
፬ ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን እንጽፍላችኋለን።
፭ ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት።
፮ ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን እውነትንም አናደርግም፤
፯ ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።
፰ ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም።
፱ በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።
፲ ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።