፳
፩ ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለማ ሳለ ማለዳ ወደ መቃብር መጣች ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች።
፪ እየሮጠችም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር መጥታ። ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም አለቻቸው።
፫ ስለዚህ ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ።
፬ ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና አስቀድሞ ከመቃብሩ ደረሰ፤
፭ ዝቅም ብሎ ቢመለከት የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ነገር ግን አልገባም።
፮ ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥
፯ ደግሞም በራሱ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ።
፰ በዚያን ጊዜ አስቀድሞ ወደ መቃብር የመጣውም ሌላው ደቀ መዝሙር ደግሞ ገባ፥ አየም፥ አመነም፤
፱ ከሙታን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ገና አላወቁም ነበርና።
፲ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቤታቸው ደግሞ ሄዱ።
፲፩ ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤
፲፪ ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች።
፲፫ እነርሱም። አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? አሉአት። እርስዋም። ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም አለቻቸው።
፲፬ ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም።
፲፭ ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት። ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው።
፲፮ ኢየሱስም። ማርያም አላት። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ። ረቡኒ አለችው፤ ትርጓሜውም። መምህር ሆይ ማለት ነው።
፲፯ ኢየሱስም። ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ። እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት።
፲፰ መግደላዊት ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች።
፲፱ ያም ቀን እርሱም ከሳምንቱ ፊተኛው በመሸ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው።
፳ ይህንም ብሎ እጆቹንም ጎኑንም አሳያቸው። ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው።
፳፩ ኢየሱስም ዳግመኛ። ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው።
፳፪ ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና። መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።
፳፫ ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው።
፳፬ ነገር ግን ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከእነርሱ ጋር አልነበረም።
፳፭ ሌሎቹም ደቀ መዛሙርቱ። ጌታን አይተነዋል አሉት። እርሱ ግን። የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላገባሁ እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም አላቸው።
፳፮ ከስምንት ቀን በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ደግመው በውስጥ ነበሩ፥ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበረ። ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው።
፳፯ ከዚያም በኋላ ቶማስን። ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው።
፳፰ ቶማስም። ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት።
፳፱ ኢየሱስም። ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው።
፴ ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤
፴፩ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።