፫
፩ ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ።
፪ መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው።
፫ ኢየሱስም መልሶ። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው።
፬ ኒቆዲሞስም። ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው።
፭ ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።
፮ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው።
፯ ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ።
፰ ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።
፱ ኒቆዲሞስ መልሶ። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አለው።
፲ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?
፲፩ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም።
፲፪ ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?
፲፫ ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።
፲፬-፲፮ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።
፲፯ ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።
፲፰ በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።
፲፱ ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው።
፳ ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤
፳፩ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።
፳፪ ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ በዚያም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ያጠምቅ ነበር።
፳፫ ዮሐንስም ደግሞ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና ያጠምቅ ነበር፥
፳፬ እየመጡም ይጠመቁ ነበር ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ አልተጨመረም ነበርና።
፳፭ ስለዚህም በዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአይሁድ መካከል ስለ ማንጻት ክርክር ሆነ።
፳፮ ወደ ዮሐንስም መጥተው። መምህር ሆይ፥ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው አንተም የመሰከርህለት፥ እነሆ፥ እርሱ ያጠምቃል ሁሉም ወደ እርሱ ይመጣሉ አሉት።
፳፯ ዮሐንስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል። ከሰማይ ካልተሰጠው ሰው እንዳች ሊቀበል አይችልም።
፳፰ እናንተ። እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፥ ነገር ግን። ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ እንዳልሁ ራሳችሁ ትመሰክሩልኛላችሁ።
፳፱ ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፤ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምጽ እጅግ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ።
፴ እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል።
፴፩ ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚሆነው የምድር ነው የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው።
፴፪ ያየውንና የሰማውንም ይህን ይመሰክራል፥ ምስክሩንም የሚቀበለው የለም።
፴፫ ምስክሩን የተቀበለ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ አተመ።
፴፬ እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራልና፤ እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና።
፴፭ አባት ልጁን ይወዳል ሁሉንም በእጁ ሰጥቶታል።
፴፮ በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።