፯
፩ ከዚህም በኋላ ኢየሱስ አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉ ስለ ነበር በይሁዳ ሊመላለስ አይወድም ነበርና በገሊላ ይመላለስ ነበር።
፪ የአይሁድም የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር።
፫ እንግዲህ ወንድሞቹ። ደቀ መዛሙርትህ ደግሞ የምታደርገውን ሥራ እንዲያዩ ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ፤
፬ ራሱ ሊገለጥ እየፈለገ በስውር የሚሠራ የለምና። እነዚህን ብታደርግ ራስህን ለዓለም ግለጥ አሉት።
፭ ወንድሞቹ ስንኳ አላመኑበትም ነበርና።
፮ ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። ጊዜዬ ገና አልደረሰም፥ ጊዜያችሁ ግን ዘወትር የተመቸ ነው።
፯ ዓለም እናንተን ሊጠላ አይቻለውም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ መሆኑን እመሰክርበታለሁና እኔን ይጠላኛል።
፰ እናንተ ወደዚህ በዓል ውጡ፤ እኔስ ጊዜዬ ገና ስላልተፈጸመ ወደዚህ በዓል ገና አልወጣም።
፱ ይህንም አላቸውና በገሊላ ቀረ።
፲ ወንድሞቹ ግን ወደ በዓሉ ከወጡ በኋላ በዚያን ጊዜ እርሱ ደግሞ በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ ወጣ።
፲፩ አይሁድም። እርሱ ወዴት ነው? እያሉ በበዓሉ ይፈልጉት ነበር።
፲፪ በሕዝብም መካከል ስለ እርሱ ብዙ ማንጐራጐር ነበረ፤ አንዳንዱም። ደግ ሰው ነው፤ ሌሎች ግን። አይደለም፥ ሕዝቡን ግን ያስታል ይሉ ነበር።
፲፫ ዳሩ ግን አይሁድን ስለ ፈሩ ማንም ስለ እርሱ በግልጥ አይናገርም ነበር።
፲፬ አሁንም በበዓሉ እኩሌታ ኢየሱስ ወደ መቅደስ ወጥቶ ያስተምር ነበር።
፲፭ አይሁድም። ይህ ሰው ሳይማር መጻሕፍትን እንዴት ያውቃል? ብለው ይደነቁ ነበር።
፲፮ ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው። ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም፤
፲፯ ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል።
፲፰ ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው በእርሱም ዓመፃ የለበትም።
፲፱ ሙሴ ሕግን አልሰጣችሁምን? ከእናንተ ግን ሕግን የሚያደርግ አንድ ስንኳ የለም። ልትገድሉኝ ስለ ምን ትፈልጋላችሁ?
፳ ሕዝቡ መለሱና። ጋኔን አለብህ፤ ማን ሊገድልህ ይፈልጋል? አሉት።
፳፩ ኢየሱስ መለሰ አላቸውም። አንድ ሥራ አደረግሁ ሁላችሁም ታደንቃላችሁ።
፳፪ ስለዚህ ሙሴ መገረዝን ሰጣችሁ፤ ከአባቶችም ነው እንጂ ከሙሴ አይደለም፤ በሰንበትም ሰውን ትገርዛላችሁ።
፳፫ የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሰው በሰንበት መገረዝን የሚቀበል ከሆነስ ሰውን ሁለንተናውን በሰንበት ጤናማ ስላደረግሁ ትቈጡኛላችሁን?
፳፬ ቅን ፍርድ ፍረዱ እንጂ በመልክ አትፍረዱ።
፳፭ እንግዲህ ከኢየሩሳሌም ሰዎች አንዳንዶቹ እንዲህ አሉ። ሊገድሉት የሚፈልጉት ይህ አይደለምን?
፳፮ እነሆም፥ በግልጥ ይናገራል አንዳችም አይሉትም። አለቆቹ ይህ ሰው በእውነት ክርስቶስ እንደ ሆነ በእውነት አወቁን?
፳፯ ነገር ግን ይህን ከወዴት እንደ ሆነ አውቀናል፤ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ከወዴት እንደ ሆነ ማንም አያውቅም።
፳፰ እንግዲህ ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር። እኔንም ታውቁኛላችሁ ከወዴትም እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እኔም በራሴ አልመጣሁም ነገር ግን እናንተ የማታውቁት የላከኝ እውነተኛ ነው፤
፳፱ እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ነኝ እርሱም ልኮኛልና አውቀዋለሁ ብሎ ጮኸ።
፴ ስለዚህ ሊይዙት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አልጫነበትም።
፴፩ ከሕዝቡ ግን ብዙዎች አመኑበትና። ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ይህ ካደረጋቸው ምልክቶች ይልቅ ያደርጋልን? አሉ።
፴፪ ፈሪሳውያንም ሕዝቡ ሰለ እርሱ እንደዚህ ሲያንጐራጕሩ ሰሙ፤ የካህናት አለቆችም ፈሪሳውያም ሊይዙት ሎሌዎችን ላኩ።
፴፫ ኢየሱስም። ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ ወደ ላከኝም እሄዳለሁ።
፴፬ ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም፤ እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም አለ።
፴፭ እንግዲህ አይሁድ። እኛ እንዳናገኘው ይህ ወዴት ይሄድ ዘንድ አለው? በግሪክ ሰዎች መካከል ተበትነው ወደሚኖሩት ሊሄድና የግሪክን ሰዎች ሊያስተምር አለውን?
፴፮ እርሱ። ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም የሚለው ይህ ቃል ምንድር ነው? ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ።
፴፯ ከበዓሉም በታላቁ በኋለኛው ቀን ኢየሱስ ቆሞ። ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ።
፴፰ በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ።
፴፱ ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና።
፵ ስለዚህ ከሕዝቡ አያሌ ሰዎች ይህን ቃል ሲሰሙ። ይህ በእውነት ነቢዩ ነው አሉ፤
፵፩ ሌሎች። ይህ ክርስቶስ ነው አሉ፤ ሌሎች ግን። ክርስቶስ በእውኑ ከገሊላ ይመጣልን?
፵፪ ክርስቶስ ከዳዊት ዘር ዳዊትም ከነበረባት መንደር ከቤተ ልሔም እንዲመጣ መጽሐፍ አላለምን? አሉ።
፵፫ እንግዲህ ከእርሱ የተነሣ በሕዝቡ መካከል መለያየት ሆነ፤
፵፬ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ሊይዙት ወደዱ ነገር ግን እጁን ማንም አልጫነበትም።
፵፭ ሎሌዎቹም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን መጡ፤ እነዚያም። ያላመጣችሁት ስለ ምን ነው? አሉአቸው።
፵፮ ሎሌዎቹ። እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም ብለው መለሱ።
፵፯ እንግዲህ ፈሪሳውያን። እናንተ ደግሞ ሳታችሁን?
፵፰ ከአለቆች ወይስ ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን?
፵፱ ነገር ግን ሕግን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው ብለው መለሱላቸው።
፶ ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ።
፶፩ ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው።
፶፪ እነርሱም መለሱና። አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ አሉት።
፶፫ እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ሄደ።