፳፩
፩ ዓይኑንም አንሥቶ መባቸውን በመዝገብ የሚጥሉ ባለ ጠጎችን አየ።
፪ አንዲትም ድሀ መበለት ሁለት ሳንቲም በዚያ ስትጥል አየና።
፫ እውነት እላችኋለሁ፥ ይህች ድሀ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች፤
፬ እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ እግዚአብሔር መዝገብ ጥለዋልና፤ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አለ።
፭ አንዳንዶቹም ስለ መቅደስ በመልካም ድንጋይና በተሰጠው ሽልማት እንዳጌጠ ሲነጋገሩ። ይህማ የምታዩት ሁሉ፥
፮ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ የማይቀርበት ዘመን ይመጣል አለ።
፯ እነርሱም። መምህር ሆይ፥ እንግዲህ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ይሆን ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ጠየቁት።
፰ እንዲህም አለ። እንዳትስቱ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች። እኔ ነኝ፥ ዘመኑም ቀርቦአል እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ እነርሱን ተከትላችሁ አትሂዱ።
፱ ጦርንና ሁከትንም በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ አስቀድሞ ይሆን ዘንድ ግድ ነውና፥ ነገር ግን መጨረሻው ወዲያው አይሆንም።
፲ በዚያን ጊዜ እንዲህ አላቸው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤
፲፩ ታላቅም የምድር መናወጥና በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር ራብም ይሆናል፤ የሚያስፈራም ነገር ከሰማይም ታላቅ ምልክት ይሆናል።
፲፪ ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ይጭናሉ ያሳድዱአችሁማል፤ ስለ ስሜም ወደ ምኵራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤
፲፫ ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል።
፲፬ ሰለዚህ እንዴት እንድትመልሱ አስቀድማችሁ እንዳታስቡ በልባችሁ አኑሩት፤
፲፭ ወደረኞቻችሁ ሁሉ ሊቃወሙና ሊከራከሩ የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና።
፲፮ ወላጆችም ስንኳ ወንድሞችም ዘመዶችም ወዳጆችም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ከእናንተም አንዳንዱን ይገድላሉ፤
፲፯ በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።
፲፰ ከራሳችሁም አንዲት ጠጉር ስንኳ አትጠፋም፤
፲፱ በመታገሣችሁም ነፍሳችሁን ታገኛላችሁ።
፳ ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ።
፳፩ የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ፥ በገጠር ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ፤
፳፪ የተጻፈው ሁሉ እንዲፈጸም ይህ የበቀል ጊዜ ነውና።
፳፫ በዚያን ወራት ለእርጕዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው፤ ታላቅ ችግር በምድር ላይ፥ በዚህም ሕዝብ ላይ ቍጣ ይሆናልና፤
፳፬ በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፤ ወደ አሕዛብ ሁሉም ይማረካሉ፤ የአሕዛብም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች።
፳፭ በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ምልክት ይሆናል፤ በምድር ላይም አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱም ድምፅ የተነሣ እያመነቱ ይጨነቃሉ፤
፳፮ ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ፤ የሰማያት ኃይላት ይናወጣሉና።
፳፯ በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።
፳፰ ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ።
፳፱ ምሳሌንም ነገራቸው እንዲህ ሲል። በለስንና ዛፎችን ሁሉ እዩ፤
፴ ሲያቈጠቍጡ ተመልክታችሁ በጋ አሁን እንደ ቀረበ ራሳችሁ ታውቃላችሁ።
፴፩ እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ።
፴፪ እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።
፴፫ ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም።
፴፬ ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፥ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤
፴፭ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና።
፴፮ እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ።
፴፯ ዕለት ዕለትም በመቅደስ ያስተምር ነበር፥ ሌሊት ግን ደብረ ዘይት ወደምትባል ተራራ ወጥቶ ያድር ነበር።
፴፰ ሕዝቡም ሁሉ ይሰሙት ዘንድ ማልደው በመቅደስ ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።