፲፮
፩ ለሰባቱም መላእክት። ሄዳችሁ የእግዚአብሔርን ቁጣ ጽዋዎች በምድር ውስጥ አፍስሱ የሚል ታላቅ ድምፅ ከመቅደሱ ሰማሁ።
፪ ፊተኛውም ሄዶ ጽዋውን በምድር ውስጥ አፈሰሰ፤ የአውሬውም ምልክት ባለባቸው ለምስሉም በሚሰግዱ ሰዎች ክፉኛ የሚነዘንዝ ቍስል ሆነባቸው።
፫ ሁለተኛውም ጽዋውን በባሕር ውስጥ አፈሰሰ፤ እንደ ሞተም ሰው ደም ሆነ፥ በባሕርም ከሚኖሩት ሕይወት ያለበት ነፍስ ሁሉ ሞተ።
፬ ሦስተኛውም ጽዋውን በወንዞችና በውኃ ምንጮች ውስጥ አፈሰሰ፤ እነርሱም ደም ሆኑ።
፭ የውኃውም መልአክ። ያለህና የነበርህ ጌታ ሆይ፥ ቅዱስ ሆይ፥ እንዲህ ስለፈረድህ ጻድቅ ነህ፤
፮ የቅዱሳንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ ደምን ደግሞ አጠጥተሃቸዋል፥ የሚገባቸው ነውና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።
፯ ከመሰዊያውም። አዎን፥ ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፥ ፍርዶችህ እውነትና ጽድቅ ናቸው ብሎ ሲናገር ሰማሁ።
፰ አራተኛውም ጽዋውን በፀሐይ ላይ አፈሰሰ፤ ሰዎችንም በእሳት ልታቃጥል ተሰጣት።
፱ ሰዎችም በታላቅ ትኵሳት ተቃጠሉ፥ በነዚህም መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ፥ ክብርንም እንዲሰጡት ንስሐ አልገቡም።
፲ አምስተኛውም ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ መንግሥቱም ጨለማ ሆነች ከስቃይም የተነሳ መላሶቻቸውን ያኝኩ ነበር፥
፲፩ ከስቃያቸውና ከቍስላቸውም የተነሳ የሰማይን አምላክ ተሳደቡ፥ ከስራቸውም ንስሐ አልገቡም።
፲፪ ስድስተኛውም ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከፀሐይም መውጫ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲሰናዳላቸው ውኃው ደረቀ።
፲፫ ከዘንዶውም አፍና ከአውሬው አፍ ከሐሰተኛውም ነቢይ አፍ ጓጕንቸሮች የሚመስሉ ሦስት ርኵሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ፤
፲፬ ምልክት እያደረጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸውና፥ በታላቁም ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ቀን ወደ ሚሆነው ጦር እንዲያስከትቱአቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይወጣሉ።
፲፭ እነሆ፥ እንደ ሌባ ሆኜ እመጣለሁ፤ ራቁቱን እንዳይሄድ እፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።
፲፮ በዕብራይስጥም አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ እስከተቱአቸው።
፲፯ ሰባተኛውም ጽዋውን በአየር ውስጥ አፈሰሰ፤ ከመቅደሱም ውስጥ። ተፈጽሞአል የሚል ታላቅ ድምጽ ከዙፋኑ ወጣ።
፲፰ መብረቅና ድምጽም ነጎድጓድም ሆኑ፥ ትልቅም የምድር መናወጥ ሆነ፤ ሰው በምድር ከተፈጠረ ጀምሮ እንዲህ ያለ ታላቅ መናውጥ ከቶ አልነበረም፤ ከሁሉ በለጠ።
፲፱ ታላቂቱም ከተማ በሦስት ተከፋፈለች፥ የአሕዛብም ከተማዎች ወደቁ። ታላቂቱም ባቢሎን የብርቱ ቍጣው ወይን ጠጅ የሞላበትን ጽዋ እንዲሰጣት በእግዚአብሔር ፊት ታሰበች።
፳ ደሴቶችም ሁሉ ሸሹ ተራራዎችም አልተገኙም።
፳፩ በሚዛንም አንድ ታላንት*ፍ1* የሚያህል ታላቅ በረዶ በሰዎች ላይ ከሰማይ ወረደባቸው፤ ሰዎቹም ከበረዶው መቅሰፍት የተነሳ እግዚአብሔርን ተሳደቡ፥ መቅሰፍቱ እጅግ ታላቅ ነውና።