2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ
፩
፩ በክርስቶስ ኢየሱስ እንደሚሆን የሕይወት ተስፋ፥ በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥
፪ ለተወደደው ልጄ ለጢሞቴዎስ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከጌታችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን።
፫ ሌትና ቀን በልመናዬ ሳላቋርጥ ስለማስብህ እንደ አባቶቼ አድርጌ በንጹሕ ሕሊና የማመልከውን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤
፬ እንባህን እያሰብሁ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ።
፭ በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስባለሁ፤ ይህም እምነት ቀድሞ በአያትህ በሎይድ በእናትህም በኤውንቄ ነበረባቸው፥ በአንተም ደግሞ እንዳለ ተረድቼአለሁ።
፮ ስለዚህ ምክንያት፥ እሳት እንደሚያቀጣጥል ሰው፥ እጆቼን በመጫኔ በአንተ ያለውን የእግዚአብሔርን ስጦታ እንድታነሣሣ አሳስብሃለሁ።
፯ እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና።
፰ እንግዲህ በጌታችን ምስክርነት ወይም በእስረኛው በእኔ አትፈር፥ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ኃይል መጠን ስለ ወንጌል አብረኸኝ መከራን ተቀበል፤
፱ ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፥
፲-፲፪ ስለዚህም ምክንያት ይህን መከራ ደግሞ ተቀብዬአለሁ፥ ነገር ግን አላፍርበትም፤ ያመንሁትን አውቃለሁና፥ የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ሊጠብቅ እንዲችል ተረድቼአለሁ።
፲፫ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር አድርገህ፥ ከእኔ የሰማኸውን ጤናማ ቃል ምሳሌ ያዝ፤
፲፬ መልካሙን አደራ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ።
፲፭ በእስያ ያሉቱ ሁሉ ከእኔ ፈቀቅ እንዳሉ ታውቃለህ፥ ከእነርሱም ፊሎጎስና ሄርዋጌኔስ ናቸው።
፲፮ ጌታ ልሄኔሲፎሩ ቤተ ሰዎች ምሕረትን ይስጥ፥ ብዙ ጊዜ አሳርፎኛልና፤
፲፯ በሰንሰለቴም አላፈረበትም፥ ነገር ግን በሮሜ ባደረ ጊዜ ፈልጎ ፈልጎ አገኘኝ፤
፲፰ በዚያን ቀን ከጌታ ምሕረትን እንዲያገኝ ጌታ ይስጠው፤ በኤፌሶንም እንዴት እንዳገለገለኝ አንተ በደኅና ታውቃለህ።